ሚያዝያ 07/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ የገበያ አለመረጋጋትን ሲፈጥሩ የነበሩ ከ5 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ንግድ ፍቃድ መሰረዝ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ቢሮው ጠቅሷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አከበረኝ ውጋገን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የህብረተሰቡ መሰረታዊ ፍጆታና ሌሎች ምርቶች ላይ የአቅርቦት እጥረትና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ባለፉት ጥቂት ወራት ሲታዩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ምርት በመደበቅና በማከማቸት፣ ያለንግድ ፍቃድ በመነገድ፣ ባዕድ ነገር ቀላቅሎ በመሸጥና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ኃላፊው ተናገረዋል።
በዚህም ከ2 ሺህ 500 በላይ ነጋዴዎች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ ከ3 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች የታሸጉ ሲሆን 11 ነጋዴዎች ደግሞ የንግድ ፍቃዳቸው መሰረዙን ነው የገለጹት።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በምክትል ከንቲባ ደረጃ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን የአቅርቦት ክፍተቱን ለመፍታትም የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ለሸማቹ እየቀረቡ ይገኛሉ።
በተለይም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት ታይቶባቸው የነበሩ የጤፍና የዘይት ምርቶች ላይ ማስተካከያ መደረጉን ነው አቶ አከበረኝ ያነሱት።
በዚህም በከተማዋ የሚገኙ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በመጀመሪያው ዙር ያስገቡት ከ59 ሺህ በላይ ኩንታል ጤፍ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በመሸጥ ላይ ነው ብለዋል።
በዚህም መሰረት የሰርገኛ ጤፍ ከ39 እስከ 41 ብር፤ ቀይ ጤፍ ከ37 እስከ 38 ብር እንዲሁም በኪሎ 50 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረው ነጭ ጤፍ አሁን ከ44 እስከ 47 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።
እጥረት ታይቶበት የነበረውን የስንዴ ዱቄት አቅርቦት በተመለከተም ከተማ አስተዳደሩ 10 ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እየደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በዘይት ላይ የታየውን የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ለማስተካከል ከተማ አስተዳደሩ ከፊቤላ የዘይት ፋብሪካ ጋር በተገባው ውል መሰረት 3 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለከተማው ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው ብለዋል።