በማንነቱ የታሰረ የለም ሲል መንግሥት አስታወቀ

ኅዳር 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የኅልውና ዘመቻ ባጠረ ጊዜ ለመቋጨት በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሻነት በማንነቱ የታሰረ አንድም አካል አለመኖሩን መንግሥት አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከአል ጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባልተፈቀደ ድርጊት የተሰማራ ማንኛውም ግለሰብ ተጠያቂ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ፖሊስ በሚደርሱት መረጃዎች መሰረት ምርመራ እንደሚያደርግ አመልክተው፤ የትኛውም ግለሰብ በብሔሩና በሌሎች ግለሰባዊ ማንነቶቹ ምክንያት አልታሰረም ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰራተኞች ታስረዋል በሚል በሚነሳው ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ “ግለሰቦቹ የታሰሩት የመንግሥታቱ ሰራተኞች በመሆናቸው ሳይሆን የአገሪቱን ሕግ ተላልፈው በመገኘታቸው ነው” ብለዋል።
የእርዳታ እህል ጭነው የገቡ ከ800 በላይ ተሽከርካሪዎች ለአሸባሪው ሕወሓት መንቀሳቀሻና ለሽብር ተግባሩ ማስፈጸሚያነት እየዋሉ መሆኑን ገልጸው፤ “መንግሥት ላይ ስሞታ የሚያቀርቡ አካላት ይህንን በተመለከተ ግን አንድም ጥያቄ ሲያነሱ አይታይም” ሲሉ ወቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ 300 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እየተጓጓዙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስና ቢቢሲ ባሉ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጨው መረጃ በሬ ወለደ ከመሆኑ በላይ ድብቅ አጀንዳ የያዘ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል::
ሮይተርስ “በኢትዮጵያ የብሔር ማንነትን የሚገልፅ መታወቂያ መያዝ ግዴታ ሆኗል” ሲል ሃሰተኛ ዘገባን እያሰራጨ እንደሚገኝ ዋልታ ከጥቂት ሰዓት በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡