በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ 600 ሄክታር መሬት መካናይዜሽን ዘዴ ሊለማ ነው

ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) – በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ 600 ሄክታር መሬት መካናይዜሽን ዘዴ ሊለማ ነው። በዞኑም አርሶ አደሮቹን በ39 ክላስተር አደራጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል::
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ የክላስተር ዘዴን መጠቀም የአርሶ የአደሩን ምርት እና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ የስንዴ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ከመሸፈን አኳያ ያለውን ጥረት ያግዛል ብለዋረል። ከስራ እድል ፈጠራ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል::
ዋልታ በጉዳዪ ዙሪያ ያነጋገራቸዉ አርሶ አደሮቹም በክላስተር እና መካናይዜሽን ምርትን ማምረት መቻላቸው ከዚህ ቀደም ከሚያገኙት ምርት አንጻር እድገት እንደሚኖረው ተናግረው በቀጣይም ሁሉንም አርሶ አደር ተሳታፊ የሚያደርግ አሰራር መፈጠር ይኖርበታል ብለዋል::
የኦሮሚያ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮም በዘንድሮው የመኸር ወቅት ስንዴን በክላስተር የመዝራት ዘዴን በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ ነው::
በዚህ መሰረትም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ 3.4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በክላስተር የመጠቀም ዘዴን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መንግለፁ ይታወሳል::
(በሄብሮን ዋልታው)