በሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው

ነሐሴ 10/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት እና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ትምህርት ቢሮ በጋራ በመሆን በሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዙሪያ ከግል ትምህርት ቤቶች ባለቤቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከኬጂ ጀምሮ የትምህርት አይነቶች እና ይዘታቸው፣ የክፍለ ጊዜ ድልድል፣ የማስተማሪያ ቋንቋ፣ የምዘና ሂደት እና ሥርዓት፣ የፈተና ይዘት እና ሌሎችም መመዘኛዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተማሪዎችን ብቁ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ የሚተገበሩ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ወጥነት ያለው የትምህረት አሰጣጥን እንዲከተሉ ይሰራል ተብሏል፡፡

6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና፣ 8ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እና 12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፋተናን በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች የሚወስዱ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የትምህርት ጥራትን ከየትኛውም ጊዜ በላይ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተመላክቷል፡፡

አዲሱ የትምህርት የሙከራ ፍኖተ ካርታ ወይም ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ላይ የጋራ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ በ2015 በጀት ዓመት ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ተብሏል።

በውይይት መድረኩ ላይ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ኃላፊዎች፣ ባለቤቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በሜሮን መስፍን