በረቂቅ የንግድ ህግ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተላከው ረቂቅ የንግድ ህግ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡

1952 ዓ.ም የወጣውና ከ60 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የቆየው የንግድ ህግ ሀገሪቱ ከደረሰችበት የንግድ እንቅስቃሴና ዘርፉ ከሚፈልገው አሰራር አንፃር ክፍተቶች ስለነበሩበት እንዲሻሻል ሆኗል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ በላይሁን ይርጋ ከዚህ ቀደም የነበረው የንግድ ህጉ እስካሁን በተግባር ያልተፈተሹ ድንጋጌዎችን መያዙ እንደ ዋንኛ ክፍተት መቀመጡንና ሌሎች ክፍተቶችም በህጉ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት በረቂቅ ህጉ ላይ ቢካተቱና ቢሻሻሉ ያሏቸውን የተለያዩ ሀሳቦች ያቀረቡ ሲሆን፣ የንግድ ህጉ አርቃቂ ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ስዩም ዮሐንስ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማም በስራ ላይ ያለው የንግድ ህግ ነጋዴ ማነው? በሚለው ላይ ትርጓሜ ሲሰጥ ጥቂት የስራ መስኮችን በማካተቱና አዲስ ለተፈጠሩ ስራዎች ዝግ በመሆኑ ረቂቁ ላይ ተሻሽሎ እንዲቀርብ መደረጉንም ዶ/ር ስዩም ተናግረዋል፡፡

በረቂቅ ህጉ ላይ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት የመሰብሰብ ሂደቱ የሚቀጥል ሲሆን፣ የተሰበሰቡ ግብዓቶች ከተካተቱበትና ማሻሻያዎች ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

(በትዕግስት ዘላለም)