በሩሲያ ዳገስታን ግዛት በተሰነዘረ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ

ሰኔ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በሰሜን ሩሲያ ዳገስታን ግዛት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ የአይሁድ ቤተ ዕምነትና ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 15 ፖሊሶችን ጨምሮ በርካታ ሲቪሎች ተገደሉ።

ትናንት እሁድ በተፈጸመው ጥቃት የጰራቅሊጦስ በዓልን እያከበሩ በነበሩ ሁለት የሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ቄስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን መገደላቸውን ቲአርቲ ወርልድ ዘግቧል።

በጥቃቱ ከ12 በላይ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን በድርጊቱ የተሳተፉ ስድስት “አሸባሪዎች” በተኩስ ልውውጡ መገደላቸውን እንዲሁም ሌሎች ታጣቂዎችም እየታደኑ መሆናቸውን በዘገባው ተጠቅሷል።

የግዛቱ አስተዳዳሪ ሰርጌ ሜሊኮቭ ባስተላለፉት መልክት ለግዛቱና ለሩሲያዊያን ከፍተኛ የሀዘን ቀን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ጥቃት አድራሾቹን በተመለከተ ከጥቃቱ ጀርባ ያለውን አሸባሪ ድርጅት እና ዓላማውን እናውቃለን ቢሉም በስም አልጠቀሱም።

በማካቻካላ እና ደርቤንት በተባሉ የሰሜን ካውካሲያን ከተሞች ትናንት በተሰነዘረው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደም ሆነ የጥቃቱ አድራሾቹ ጥያቄም ምን እንደሆነ በግልፅ የተባለ ነገር የለም።

ከሶስት ወራት በፊት ሞስኮ አቅራቢያ በሙዚቃ ድግስ ላይ በተሰነዘረ የሽብር ጥቃት 133 ሰዎች መገደላቸውንና ለጥቃቱም መቀመጫውን አፍጋኒስታን ያደረገው በኮራሳን ግዛት የእስላሚክ ስቴት (አይኤስኬፒ) የሚባል ቡድን ኃላፊነት መውሰዱ ይታወቃል።

በደረሰው ጥቃት በግዛቲቱ የሶስት ቀናት ሀዘን የታወጀ ሲሆን ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብና የመዝናኛ ዝግጅቶች እንዲሰረዙ ተደርጓል ተብሏል።