በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኔት ወርክ ውጪ ሆኑ

ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ችግር በርካታ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ከኔት ወርክ ውጪ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ችግር በዓለም ዙሪያ ያሉ የዊንዶውስ ኮምፒዩተሮች በድንገት መጥፋታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህን ተከትሎም የሚዲያ ተቋማት፣ ባንኮች፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ተቋማትና አየር መንገዶች ስራ ከመስራት መስተጓጎላቸው ተሰምቷል፡፡

የበርካታ አውሮፕላኖችም ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት ለማረፍ መገደዳቸውን የስካይ ነውስ ዘገባ አመላክቷል፡፡

አውስትራሊያ በስፋት ከተጠቁት ሀገራት መካከል ስትሆን እስራኤል፣ ህንድ፣ ሲንጋፖር እና አንግሊዝ ችግሩ እንደገጠማቸው አስታውቀዋል።

የለንደን የአክሲዮን ገበያም የዚህ ችግር ሰለባ መሆኑ ታውቋል፡፡ የአሜሪካ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን እንዲሰረዙ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

ችግሩ የገጠማቸው ተቋማት የማይክሮሶፍት 365 መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

የአውስትራሊያ ብሄራዊ ደህንነት ጉዳዩን እየተመለከተው መሆኑን ገልጾ ክስተቱ የሳይበር ጥቃት ነው ለማለት የሚያስችል መረጃ ግን እስካሁን አለመኖሩን አስታውቋል፡፡