በሰሜን ሸዋ ዞን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ግንቦት 14/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡

በዞኑ በሚገኙ በአቦቴ እና በወረጃርሶ ወረዳዎች በስፋት በመንቀሳቀስ ህበረተሰቡን ሲዘርፉ እና ሲያሰቃዩ በነበሩት የሸኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ በመወሰዱ በአሁኑ ወቅት በአካባቢዎቹ ሰላም መስፈኑ ተገልጿል።

በዞኑ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማስፈን በሽብር ቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የገለፁት የጥምር ፀጥታ አካላት አስተባበሪ እና በኮማንዶ ክፍለ ጦር የሬጅመንት ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ታሄል ሬድ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ አመርቂ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ ዋና አዛዡ ገለፃ እስከ አሁን በተደረጉ ዘመቻዎች 44 የሽብር ቡድ አባላት ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው አምስት ተማርከዋል፡፡

በተጨማሪም 18 የተለያዩ መሳሪያዎች እና የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምበት የነበረም 19 ኩንታል እህል በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

233ቱ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የሰጡ መሆናቸውን ሌተናል ኮሎኔል ታሄል ገልፀዋል።

ከአከባቢው ህብረተሰብ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአባገዳዎች ጋር በመሆን በተሰራው የተቀናጀ ተግባር የተገኘው ድል አበረታች ነው ያሉት ደግሞ የወረጃርሶ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አየለ መንግስቱ ናቸው።

ከህብረተሰቡ የተወከሉ የአከባቢው ሽማግሌዎች እና አባገዳዎችን ወደ ጫካ በመላክ ከታጣቂዎቹ ጋር በተደረገው ድርድር እና ውይይቶች በርካታ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች በየቀኑ በሰላማዊ መንገድ በአካባቢው ለተሰማሩት የፀጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸው በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም መስፈን ችሏል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ አመላክቷል።