በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ታስቦ እንደሚውል ተገለጸ

ጥቅምት 21/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው የክህደት ተግባር እና ጥቃት ጥቅምት 24 ታስቦ እንደሚውል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመራ ቆይቶ መቐለ ከመሸገ በኋላ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሁሉንም አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ነበር፡፡
ይህ ሳይሳካለት ሲቀር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያስችለኛል ያለውን እና ላለፉት 20 ዓመታት ሙሉ ሲጠብቀው በኖረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ታሪክ የማይረሳውን አጋጣሚ ለማሰብ እና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆንን ለማረጋገጥ “አልረሳውም እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ” በሚል መርህ ቃል በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል በተለያዩ ስነሥርዓቶች ተከብሮ እንደሚውል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ቀኑ ለ45 ሰከንድ የህሊና ፀሎት በማድረግ፣ ሻማ በማብራት እና የደም ልገሳ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ እንደሚከበር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ጥቅምት 24 የአሻባሪው ቡድን የህዝብ ማእበል በማንቀሳቀስ እና በየቦታው የሰገሰጋቸውን ጀሌዎች በማሰማራት ኢትዮጵያዊያንን እየገደለ ንብረታቸውን እየዘረፈ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ቃል የሚገባበት እና በአንድነት የሚቆምበት አጋጣሚ ተደርጎም ይወሰዳል ተብሏል፡፡
በሚልኪያስ አዱኛ