በሰበታ ከተማ 75 ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ነው

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) በሰበታ ከተማ አስተዳደር 75 ፕሮጀክቶች ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በጀት እየተሰሩ መሆናቸው ተነገረ።
በከተማዋ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ 26 ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ 49 ፕሮጀክቶች ባጠቃላይ 75 ፕሮጀክቶች ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸው እየተሰሩ መሆኑን የሰበታ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጫላ ለሚ ተናግረዋል።
ይህም በጀት ከቋሚ በጀትና ከማዘጋጅያ ቤት የተበጀተ መሆኑንም ገልፀዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የተለያዩ ዘርፎችን በስራቸው ያቀፉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሆስፒታል፣ የቡዑረ ቦሩና ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤቶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ድችና ሌሎችንም ያካተተ ነው።
የፕሮጀክቶቹ የሥራ ሂደት ላይ የተለያዩ ችግሮች እያጋጠማቸው መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው ከነዚህ ችግሮች መሀከል የዲዛይን ችግር፣ የገበያ ግሽበትና ሌሎችም ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይሁንና እነዚህን ችግሮች ፈትቶ የሥራውን ሂደት ለማፍጠን ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በታምራት ደለሊ