በሰባት ክልሎች ለሚገኙ ዘጠኝ የግብርና ምርቶች የምርት መለያ ሥያሜ ተሰጠ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) በሰባት ክልሎች የኅብረት ሥራ ማኅበር አባላት ለሚመረቱ ዘጠኝ የግብርና ምርቶች የምርት መለያ ሥያሜ (ብራንድ) መስጠቱን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቋል።
የምርት ሥያሜ (ብራንድ) የተሰጣቸው የቦንጋ በግ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለውዝ፣ የሀረሪ አምባ ንጉሥ ማንጎ፣ የመቂ ባቱ ሽንኩርት፣ የአፋር ቴምር፣ የሀላባ በርበሬ፣ የአፍዴራ ጨው፣ የአፍዴራ ነጭ ፍየል እና የሶማሌ ቀላፎ ሽንኩርት ናቸው።
ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሥያሜው ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ገበያም ተፈላጊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
የምርት ሥያሜ የተሰጣቸውን ምርቶች በከተሞች ታላላቅ አደባባዮች ላይ እንዲተዋወቁ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ፤ ስያሜው ምርቶቹ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙና ገበያ በማረጋጋት ረገድ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ያስችላል ነው ያሉት።
ጳጉሜ 2 ቀን 2014 ዓ.ም በሚከበረው የአምራቾች ቀን የምርት ስያሜ (ብራንድ) የተሰጣቸው ምርቶች በሚሊኒየም አዳራሽ ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የአርባምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ ድንች የምርት ስያሜን (ብራንድ) ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።