በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ

የካቲት 25/2014 (ዋልታ) በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራና 16 ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአርባ ምንጭ ሳምንታዊ መግለጫቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በሳውዲ እንግልት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቅርቡ ወደ አገራቸው እንዲገቡ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በዩክሬን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ በተመለከተ የጀርመን ኤምባሲ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም አንስተዋል።
ባለፈው ሳምንት የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በአገራቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከራቸውንም አመልክተዋል።
በምክክራቸውም በቅርቡ ስለተቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለፃ እንደተደረገና አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር በኩል አሁንም እያደረገ ስላለው ትንኮሳ በዝርዝር መነገራቸውን ጠቁመዋል።
በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ጋር ስለሶማሊያ ምርጫ እና በአካባቢው ስለምንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ውይይት ተደርጓልም ነው ያሉት።
የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ብለዋል በመግለጫቸው።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባለፈው ሳምንት 139 ኢትዮጵያዊያንን ከኬኒያ መመለስ መቻሉንም የገለጹት አምባሳደር ዲና ለዚህም የኬኒያ መንግሥት ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ከተቋቋመ ለሁለተኛ ጊዜ “ኢትዮጵያን ከውጭ ጫና እንዴት ነፃ እናድርግ” በሚል ያዘጋጀው መድረክ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አራያ መሆን የሚችል ነውም ብለዋል፡፡
ሜሮን መስፍን (ከአርባምንጭ)