በስኬቶቻችን ላይ በመመስረት በሁሉም ዘርፎችና መስኮች እድገታችንን ማፋጠን ይኖርብናል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 9/2016 (አዲስ ዋልታ) በስኬቶቻችን ላይ በመመስረት እና በሰፊ የሰው ኃይላችን በመደገፍ በሁሉም ዘርፎች እና መስኮች እድገታችንን ማፋጠን ይኖርብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በግብርና ዘርፍ ያገኘናቸው ስኬቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍም በመደገም ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የተካሄደውን የመዋቅር እና የአመራር ለውጥ ተከትሎ ተቋሙ ሪቨርስ ኢንጂነሪንግ ዘዴን በመጠቀም የተለያዩ መሳሪያዎችን፣ ሮኬቶችን እና ታንኮችን ለማምረት አስደናቂ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

እያሳደግናቸው ያሉ አቅሞች ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየረዱን ለሀገራችንም ሆነ ለአህጉራችን ተስፋ እየሆኑ ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል።