በስድስት ወራት ብቻ ከ2 ሺሕ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሞከራው ተገለጸ

ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)

ጥር 14/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ2 ሺሕ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሞከራቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) የተቃጣው የሳይበር ጥቃት ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ቁጥሩ ማሻቀቡን ጠቁመው የዘንድሮ የሳይበር ጥቃት ቁጥር ባሳለፍነው ዓመት በሙሉ ከተደረገው ጥቃት እኩል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ከ2 ሺሕ 800 በላይ አደገኛ የሳይበር ጥቃቶች ተሰንዝረው ሙሉ በሙሉ ማምከን መቻሉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከዚህ ቁጥር ያላነሰ ተሰንዝሮ ማምከን እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ቴክኖሎጂው ባደገ ቁጥር የሳይበር ጥቃት ለማድረግ አላማቸውን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ ወንጀለኞች ተበራክተዋል፡፡

በአገር ላይ ከፍተኛ ወንጀል ሊፈጽሙ የሚፈልጉ አካላት በአካል ወደ አገር መግባት ስለማይችሉ የሳይበር ጥቃት ከፍተኛ መሣሪያቸው መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የሚሞክሯቸውን ጥቃቶች ማምከን ባይቻል ኖሮ ምናልባት አሁን የምናያት ዓይነት አገር ላትኖረን ትችል ነበር ሲሉም የጥቃቶቹን አሳሳቢነት ጠቁመዋል፡፡

በየቀኑ እየጨመረ በሚገኘው ቴክኖሎጂ ምክንያት በአገርም ላይ ሆነ በተለያዩ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስ ኤጀንሲው የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ቀን ከሌት ሠራዊት ሆኖ አገሩን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝም መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡