በሸንኮር ወረዳ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት ጋር በተያያዘ የምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የሀረሪ ክልል ጸጥታ ም/ቤት አስታወቀ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በትንሣኤ በዓል እለት በሸንኮር ወረዳ ዮድ ካፌና ሬስቶራንት ፀረ ሰላም ኃይሎች በወረወሩት ቦንብ ቦታው ላይ በነበሩ ዜጎች ላይ በደረሰው የአካል ጉዳት ማዘኑን ገልጾ ከጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር የማድረግ እና የምርመራ የማካሄድ ተግባር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት በአፋጣኝ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ በቁርጠኝነት እንደሚፈጸምና መሰል ተግባራት እንዳይደገሙ እንደሚሰራ ገልጿል።

ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር እና በክልሉ ሰላም እንደሌለ አድርገው በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቅስቀሳ በሚያደርጉ እና የሀሰት መረጃ በሚያሰራጩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ የፀጥታው ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት በክልሉ ሰላም እንዲጠናከር በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናልም ነው የተባለው።

በሌላ በኩል በክልሉ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው ሸዋል ኢድ እንዲሁም የኢድ አልፈጥር በዓላት ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

ለሥራው ውጤታማነት ግብርኃይል ተቋቁሞ በየጊዜው በክልሉ የፀጥታው ምክር ቤት እየተገመገመ መልካም ተግባራት እንዲጎለብቱ እና በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችም በአፋጣኝ እንዲታረሙ እየተደረገ መሆኑን ተመላክቷል።

መጪዎቹ በዓላትም ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ በተለይ የፀጥታ ኃይልን በማጠናከር፣ በተመረጡ አካባቢዎች ተገቢውን ፍተሻና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ሕዝብን በላቀ ደረጃ በማቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

በመሆኑም የክልሉ ሕዝብ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ በሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል የሚኖሩባት ክልል መሆኗን በተግባር እንዲያረጋግጥ ተጠይቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኢድ አልፈጥር በዓልን በሀገር ቤት እንዲያከብሩ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በክልሉም በዓሉ የተሳካ እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ተብሏል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!