በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው ደባርቅ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቀቀ

 

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ሙሉ ወጪ የተገነባው ደባርቅ ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግንባታ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በቀጣይ ወር ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በ13 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ይህ ትምህርት ቤት 18 መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፅሀፍት፣ ቤተ ሙከራዎች፣ የአስተዳደር ህንፃ፣ መጸዳጃ ቤትና ክሊኒክ ያሟላ ነው፡፡

የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ፈንታ እንዳሉት÷ በቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው የተገነባው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በከተማው የሚታየውን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግር የሚፈታ ነው ፡፡

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ዘመን ተሻጋሪ እና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ጥራት ያላቸውን የግንባታ ቁሳቁሶችን ከመጠቀም ጀምሮ ተገቢ የሆነ የባለሙያ ክትትል ተደርጎለታል ተብሏል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመረዳት እድሉን መስጠቱ በከተማ አስተዳደሩ ተማሪዎችና መምህራን ስም ምስጋና ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈትቤት ኃላፊ ትምህርት ቤቱ አዲስ በመሆኑ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበርና ሌሎች ግብአቶችን ለማሟላት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግብአት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት የሚመለከተው የመንግስት ተቋም፣ የአካባቢው ማህበረሰብና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ድጋፍ እንዲያደርጉም የትምህርት ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል :: (ምንጭ ፡- የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ )