በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀመረ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዘርፈ ብዙ በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታን አስጀመሩ፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ለሌላው የከተማው አካባቢዎች ተሞክሮ መሆን የሚችሉ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄ ባለባቸው ስድስት ዋና ዋና ዘርፎች የልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጓል፡፡
ከነዚህም ውስጥ የቤት አቅርቦት፣ የዳቦ አቅርቦት ማሻሻልና ማእድ ማጋራት፣ የከተማ ግብርና፣ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ የአገልግሎት ማሻሻል፣ የእሁድ ገበያ ማስፋፋት ይገኙበታል፡፡
የቤት ፕሮጀክቶቹ በተለይም ከነበረው ያረጁ ቤቶች እድሳት በተጨማሪ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ ኅብረተሰቡ ከአካባቢውና ማኅበራዊ ህይወቱን ከመሰረተበት አካባቢ ሳይፈናቀል በ2 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ የዝቅተኛ ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ የሚመጥን ዋጋ ያለው እና ዛሬ የተጀመሩት 4 የጋራ መኖርያ ቤቶች በአጠቃላይ እስከ 200 ቤቶች የሚይዝ ግንባታ ነው ተብሏል፡፡
ይህም ከከተማው እድገት ጋር የሚጣጣም እና ከግል ሴክተሩ ጋር በመተባበር የሚተገበር ባለ 9 ወለል አዲስ አይነት የተገጣጣሚ ቤቶች ነው የተባለው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች 8 የዳቦ ፋብሪካዎችን በተመሳሳይ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የሚገነቡ ሲሆን 2 የምገባ ማእከላትን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች የሚመገቡባቸው እና 32 የሸገር ዳቦ ማቅረቢያ ቦታዎች በይፋ ግንባታ በይፋ ተጀምረዋል፡፡
በሌላ በኩል በክፍለ ከተማው የከተማ ግብርናን በስፋት በመተግበር በመሃል ከተማ የጓሮ አትክልት ሰዎች ራሳቸውን በምግብ የሚችሉበትን መንገድ በስምንት ሞዴል ቦታዎች የሚተገበር ይሆናል፡፡
በተጨማሪም በክፍለ ከተማው ለመላው የአዲስ አበባ ሞዴል የሚሆን ከተማውን ውበት የሚጠብቀውን ቡራቡሬ የሆነውን የህንፃ ቀለም በማስተካከል ለከተማው የሚሆን ተመሳሳይ ብራንድ ቀለም በመፍጠር አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስና ውብ እንድትሆን የሚያስችል ሞዴል ሥራ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በነዚህ ፕሮጀክቶች ከተማዋ የሚገባትን እድገት እንድታገኝና በዚህ በእድገትና ለውጥ ውስጥ ደግሞ የዜጎች ህይወት አብሮ የሚቀየርበት ሥራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ እነዚህ ሥራዎች ያከበረንን ሕዝብ መልሰን የምናከብርበት በድምፁ የመረጠንን ሕዝብ የምንክስበት ነው ያሉ ሲሆን በተለይ ከቤቶች ግንባታ አንፃር የከተማው ነዋሪ ሌላው ቢቀር የመኖርያ ቤት ባለቤት መሆን እንኳን ባይችል ተከራይቶ መኖር የሚችልባት ከተማ ማድረግ አለብን ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።