በቅዱስ ላሊበላ ገዳም ሥር የሚተዳደሩ ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል ተባለ

ሚያዝያ 4/2014 (ዋልታ) በኮቪድ-19 እና በጦርነቱ ሳቢያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በቅዱስ ላሊበላ ገዳም ሥር የሚተዳደሩ ካህናትና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተገለፀ።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሁን ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ የገዳሙ አስተዳዳሪና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት መግለጫ ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አካባቢው አንድም ቱሪስት እየመጣ ባለመሆኑ ከ10 ሺሕ በላይ ካህናትና ቤተሰቦቻቸው ለችግር ተዳርገዋል።
ከ100 በላይ ሰራተኞች፣ 800 የአብነት ተማሪዎችና ከ200 አረጋዊያን እንዲሁም ወላጅ አልባ ሕጻናት በችግር ውስጥ መሆናቸውን የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ስላሴ መዝገቡ ገልጸዋል።
ገዳሙ ከዚህ ችግር እንዲወጣም መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ከሚሴ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ በበኩላቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትሏቸው ቅርሶች ዋነኛ ነው ብለዋል።
ሆኖም አሁን ላይ ገዳሙ ያለበትን ሁኔታ በመረዳት ሁሉም ድጋፍ ሊያደረግ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻም በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በአካባቢው የመብራትና የውሃ አገልግሎት ባለመኖሩም ሕዝቡ ለተጨማሪ ጉዳት እየተዳረገ እንደሆነ በመግለጫው መገለጹን ኢዜአ አስነብቧል።