በበዓላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ቁጥጥር የሚያደርግ ግብረ ኃይል ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ

ታኅሣሥ 19/2015 (ዋልታ) በገናና ጥምቀት በዓላት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አዳነ ሱሌ የምርት አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም እንዳይከሰት ከበዓላቱ በፊት በልዩ ትኩረት መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላትም ከወዲሁ ምርቶቹን እንዲያከፋፍሉና በተመደቡባቸው ቦታዎች እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከምርት አቅርቦቱ ጎን ለጎን የጥራት፣ የዋጋ፣ የመጠን እንዲሁም ሕጋዊነት ክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ይሠራል ብለዋል፡፡

ከቢሮው ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው በዓላቱን ታሳቢ በማድረግ ለሸማቹ ሕብረተሰብ የሚቀርቡ የድጎማ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡