በባኮ-ሻምቡ መንገድ የተፈጠረውን የመንሸራተት አደጋ ተከትሎ የትራፊክ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው – ባለስልጣኑ

ነሃሴ 06/2013 (ዋልታ) – በባኮ-ሻምቡ መንገድ ያጋጠመውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ የተፈጠረውን የትራፊክ መስተጓጉል ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በአካባቢው ያለው የአፈር አይነት ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በመሆኑ እንዲሁም ሰሞኑን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ከባኮ 26 ኪሎሜትር ርቅት ላይ አላቱ መዳረሻ ሶስት ቦታዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ማጋጠሙ ተገለፀ፡፡

ይህን ተከትሎም በትራፊክ ፍሰቱ ላይ መጠነኛ መስተጓጎል መከሰቱን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ እና የትራፊክ ፍሰቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አሰቸኳይ ጥገና እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

አሰቸኳይ ጥገናው በፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን የትራንስፖርት ፍሰቱ መንቀሳቀስ ጀምሯል ተብሏል፡፡