በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከ69 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ተገለፀ

ታኅሣሥ 28/2014 (ዋልታ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን በፀጥታ ችግሮች ምክንያት ከ69 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የ6 ወራት አፈፃፀሙ ላይ ሲወያይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ እንዳሉት የፀጥታ ችግሩ በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ በመቋቋም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቢንያም መንገሻ በበኩላቸው በፀጥታ ችግሩ 114 የመጀመሪያና 5 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን 94 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል መውደማቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም በትምህርት ገበታቸው መገኘት የነበረባቸው ከ69 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አርጓቸዋል ማለታቸውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት መረጃ አመልክቷል፡፡