በተለምዶ የቁጥር ግምት ተብሎ የሚታወቀው የጨዋታ አይነት ህገወጥ ነው – የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር

ግንቦት 15/2015 (ዋልታ) በተለምዶ የቁጥር ግምት ተብሎ የሚታወቀው የጨዋታ አይነት ህገወጥ መሆኑን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ጉዳዩን አስመልከቶ ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ንዋይ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሁለት አላማዎች እንዳሉት ገልጸው ከነዚህም ውስጥ የተለያዩ ሎተሪዎችን ለገበያ በማቅረብ ከወጪ ቀሪ የተጣራ ትርፉን ለመንግስት ገቢ ማድረግ የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ደግሞ ፍቃድ ለሚያስፈልጋቸው የዕድል ጨዋታዎች ፍቃድ መስጠትና ህገወጥ አጫዋቾችን መቆጣጠር እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በሁለተኛው አላማው ፍቃድ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ለቶምቦላ ሎተሪ ፍቃድ፣ አገልግሎታቸውን ወይም ምርታቸውን በሽልማት ለማስተዋወቅ ለሚጠቀሙ ድርጅቶች (Promotion lottery)፣ ለቢንጎ ሎተሪ እና ለቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አስተዳደሩ አሁን በከተማው እየተንሰራፋ ለሚገኘው የቁጥር ግምት አጫዋቾች ምንም አይነት ፍቃድ እንዳልሰጠና ህገ ወጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የገንዘብ ነክ ነገሮችን የማጫወትና ፍቃድ የመስጠት መብት ያለው በብቸኝነት የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ ሎተሪ በራሱ ዝም ብሎ ፍቃድ የሚሰጥባቸው ሳይሆኑ ማህበራዊ እሴታቸውንም ከግምት የሚያስገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከፖሊስ አካላት ጋር በመሆን ህግ የማስከበር ስራ እየሰራ እንደሚገኝና ባለፉት ሦስት ወራት ገደማ 151 ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ ሀና ማርያም፣ ፈረንሳይ እና ቀጨኔ እርምጃ ከተወሰደባቸው አካባቢዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

የቤቲንግ ፍቃድ ኖሯቸው ይህን ጨዋታ የሚያጫውቱ ሆነው ከተገኙም ፍቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡

በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት ህገ ወጥ ሎተሪ በሚያካሂዱ አካላት ላይ ከ3 እስከ 5 ዓመት የእስርና ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ የገንዘብ ቅጣት እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም አስተዳደሩ እንዲህ አይነት የህገ ወጥ ጨዋታዎች በሚበዙበት አካባቢ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ የጨዋታ አይነት ህገ ወጥ መሆኑ ታውቆ የፖሊስ አካላት ህግ እንዲያስከብሩና ህብረተሰቡም እንዲህ አይነት አጫዋቾችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲያቀርብ የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ንዋይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሳሙኤል ሙሉጌታ