በተለያዩ ክልሎች የተካሄደው 6ኛ ዙር ቀሪና ድጋሚ አገራዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቀቀ

ሰኔ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ዛሬ ያካሄደው ስድስተኛ ዙር ቀሪና ድጋሚ አገራዊ ምርጫ በሰላም ተጠናቀቀ።

በክልሉ ገዋኔ ወረዳ በተቋቋሙ 45 የምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ ያለምንም ችግር በነፃና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈልጋቸውን ዕጩዎች መምረጡ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓትም ምርጫው የሕዝብና የተመራጮች እንዲሁም የምርጫ ታዛቢዎች በተገኙበት የድምፅ ቆጠራ ተጀምሯል። በወረዳው በተካሄደው ምርጫ 225 የምርጫ አስፈፃሚዎች መሳተፋቸውም ተመላክቷል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመስቃን እና ማረቆ ምርጫ ክልል ሁለት ጣቢያዎች የድምፅ መስጠት መርኃ ግብር ተጠናቋል።

በ169 የምርጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት በጀመረው የምርጫ ስርዓት ቀኑን ሙሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በምርጫ ጣቢያዎቹ ታዛቢዎች በተገኙበት የድምፅ ቆጠራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የምርጫ ሂደቱን በማስተባበር በአጠቃላይ 845 የምርጫ አስፈፃሚዎች መሳተፋቸውም ተገልጿል።

በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያዎች የተሰበሰቡ ድምፆች ወደ ማዕከል እንደሚላኩና በቀጣይም በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ውጤቶች ይፋ ይደረጋሉ ተብሏል።

በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ምርጫ ክልል ሁለት ዛሬ ሲካሄድ የዋለው ድጋሚ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን የምርጫው አስተባባሪ አስታውቀዋል።

የምርጫው አስተባባሪ ኃይለየሱስ ወርቁ እንደገለጹት በከተማው በተቋቋሙ 123 ምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ ያለምንም ችግር በነፃና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈልገውን ዕጩ መርጧል።