በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ምሁራን ለአገር የመቆም ጥሪ አስተላለፉ

ሚያዝያ 20 /2013 (ዋልታ) – በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ምሁራን ለአገር የመቆም ጥሪ አስተላለፉ።
ቁጥራቸው 70 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ምሁራኖች ባስተላለፉት ለአገር የመቆም ጥሪ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በረጅም እድሜዋ ብዙ ጊዜ ታማ ድናለች።
“ኢትዮጵያ ልጆቿ አልፎ አልፎ ተጣልተዋል፤ ተዋግተዋልም፤ ግን በጠባቸው መካከል እንኳን ለአገራቸው ተባብረዋል እንጂ፣ ምንጊዜም ሕልውናዋን ለጠላት አሳልፈው ሰጥተው አያውቁም” ያለው የምሁራኑ የጋራ መግለጫ፤ ኢትዮጵያን የውጭ ጠላቶች በተለያየ ጊዜ ሊደፍሯት ሞክረው ሁሉም አፍረው መመለሳቸውን አስታውሷል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህም ለሌሎች የነጻነት ምሳሌ ሆና በኩራት ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፏን ገልጿል።
“በአሁኑ ጊዜ ያለው ተቀዳሚ ቅራኔ ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚሉና አትፈርስም በሚሉ መካከል ያለ ፍልሚያ ነው” በማለት ገልጾ፣ “አደገኛ የውስጥ ግጭትና የውጭ ከበባና ዛቻ ባለበት በዚህ ወቅት ልዩነት ላይ በማተኮር የምንበታተንበት ሳይሆን የተነሳብንን አደጋ በጥልቀትና አርቆ በማሰብ መርምረን በምን መልክ እንመክታለን በሚለው ላይ ተቻችለን መተባበር ነው” ሲሉ ምሁራኑ ባወጡት የጋራ መግለጫ ጥሪ አስተላልፈዋል።