በተደረገልን ድጋፍ ካጋጠመን የምግብ እጥረት እየወጣን ነው – የሽሬ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች

የካቲት 18/ 2013 (ዋልታ) – ከመንግስት እያገኙ ባለው ሰብዓዊ ድጋፍ ካጋጠማቸው የምግብ እጥረት ችግር እየወጡ መሆናቸውን በትግራይ ክልል የሽሬ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በሽሬ ከተማና አካባቢዋ በሕግ ማስከበሩ ሂደት ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎችና ከሌላ አካባቢ ተፈናቅለው ለተጠለሉ ዜጎች መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ ነው፡፡

ድጋፉን እያገኙ ያሉት ነዋሪዎች ካጋጠማቸው ችግርና ረሃብ እየተላቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በግለሰብ ደረጃ ለሁለት ወራት 30 ኪሎ ግራም ስንዴና ዘይት መውሰዳቸውን ተናግረው እርዳታውን ማግኘታቸው የነበረባቸውን የምግብ እጥረት ችግር እየፈታላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የድጋፍ አቅርቦቱ የቤተሰብ ብዛትን ታሳቢ በማድረግ በፍትሐዊነት እየተዳረሰ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ ኑሯቸው ወደ ቀደመው ሁኔታ እስከሚመለስና ራሳቸውን ችለው መስራት እስከሚጀምሩ ድጋፉ እንዲቀጥልም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍ ያገኙት ተፈናቃዮች በበኩላቸው መንግስት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ ዞን ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋዊ “ከመንግስት የመጣውን ዕርዳታ በወቅቱ ለነዋሪዎች ለማድረስ እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡

እየተሰጠ የሚገኘው ሰብዓዊ ድጋፍ የሽሬ ከተማ ነዋሪዎችን፣ ተፈናቃዮችና 15 የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ በሚገኙ ሌሎች ወረዳዎችም ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሽሬ ከተማ የሚገኙ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡