በትምህርት ጥራት ምዘና ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው

በትምህርት ጥራት ምዘና ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ

ነሐሴ 24/2013 (ዋልታ) – ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በትምህርት ጥራትና ምዘና ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) መንግስት ባለፉት ሦስት አመታት የትምህርት ጥራት ለማምጣት ማነቆዎች ናቸው ያላቸውን የህግ ማእቀፎች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመለየት ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ጥራት ያለውና በአለማቀፍ ደረጃ በየትኛውም መስክ ተወዳዳሪ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ተቋማትም ጥራት ያለውና በየትኛውም ደረጃ ብቁ የሆኑ ዜጋ ለማፍራት በተጠያቂነት መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጥራትና ምዘና ማዕከል ግንባታ እየተካሄደ እንደሆነና ተግዳሮት ናቸው የተባሉ የህግ ማእቀፎችን ለማሻሻል እየተሰራ እንደሆነም ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ከአምስት መቶ በላይ ተሳታፊዎት ተገኝተዋል።

ውይይት ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

(በሳራ ስዩም)