በትግራይ መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች እየተሰራጩ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ

 

ከ71 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ተልከው እየተሰራጩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር፣ ኤጀንሲዎቹ እና የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከሰብዓዊና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ላይ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡

በተጎዱ አካባቢዎች ያለው የህብረተሰብ ጤና እና ደህንነት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

መንግስት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የድንገተኛ ምላሽ እየሰጠና ወገኖች ወሳኝ የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ ላለፉት በርካታ ሳምንታት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ለደረሰው አስቸኳይ ሁኔታ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ትግራይ መላኩ አይዘነጋም፡፡

እስካሁን ከ71 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና ግብዐቶችን በክልሉ ለሚገኙ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ማዕከላት ተልከው ለሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ጤና ተቋማት የሚሰጡት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ከሕክምና አቅርቦቶችና መድኃኒቶች በተጨማሪ አምቡላንሶችን ጨምሮ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በማህበረሰቡ ውስጥ የበሽታ ቅኝትና የተንቀሳቃሽ ክሊኒከ አገልግሎቶችም በአንዳንድ አካባቢዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እና የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሮች ከጥር 4 እስከ ጥር 5 ቀን 2021 በሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል የተመራው የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ቡድን ልዑክ አካል ነበሩ፡፡

የልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ ከጊዜያዊው የትግራይ ክልል አስተዳደር ጋር በመወያየት ፈጣን ምላሽ ለሚሹ የጤና እና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቅድሚያ የሰጡ ሲሆን ውጤታማ ምላሽ ለመስጠትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሰራት ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡