በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 እንደሚሰጥ ተገለጸ

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ነሐሴ 6/2015 (አዲስ ዋልታ) በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሳይፈተኑ የቀሩ ተማሪዎችን ለማስፈተን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በክልሉ የአጠቃላይ መደበኛ ትምህርት ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል።

በዚህም በተለይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ቅዳሜን ጨምሮ በሳምንት ለስድስት ቀናት ዋና ዋና ትምህርቶች ላይ ያተኮረ ትምህርት እንዲወስዱ መደረጋቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

እንደቢሮው ገለጻ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ለፈተና የሚያበቃ የማጠናከሪያ ትምህርት እየወሰዱ ይገኛሉ።

የትምህርት ሚኒስቴርም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና የሚያበቃቸውን ትምህርት እንዲያገኙ ከፍተኛ የቅንጅት ስራ መሰራቱን አስታውቋል።

የትምርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በተፋጠነ የትምህርት አሰጣጥ ለፈተና ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም በክልሉ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2/2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲዎቹ መምህራንን እየጠሩ መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ሂደት ወደ መደበኛ ሂደት እየተመለሰ ነው ብለዋል።