በትግራይ 1.6 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ ተችሏል- የሰላም ሚኒስቴር

በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ የማድረስና መልሶ የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡

የሚኒስትሮች አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ማስተባበሪያ ማዕከል ሰብሳቢ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያሽፈልጋቸው ዜጎች እየተደረገ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ ለመገናኛ ብዙኃን ገለጻ አድርገዋል፡፡

በትግራይ ክልል የህግ ማስከበሩን ተከትሎ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የእለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቆ ድጋፉን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ እስካሁን 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ለሚሆኑት ዜጎች ከ305 ሺህ በላይ ኩንታል የእህል ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ድጋፍ በማድረግ ሂደቱ የተሳተፉ ሲሆን እስካሁን 22 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል በጥምረት እና 69 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ለሴፍቲኔት ተረጅዎች ለማድረስም በሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ በክልሉ የኤሌትሪክ፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን እና የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ ስለነበር ስራውን አስቸጋሪ አድርጎት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በክልሉ መሻሻሎች በመኖራቸው ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 71 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎ የመድሃኒት አቅርቦት ለማድረስ ጥረት መደረጉንና የውሃ መስመሮች እስከሚጠገኑ በቦቴ ውሃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ 92 የሚሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ የማሰራጫ ማዕከላት አሉ ያሉት ሚኒስትሯ እስካሁን የስደተኞች ካምፕን ጨምሮ 80 ማዕከላት ላይ ማድረሽ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል በታጣቂዎች ጥቃት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከ104 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከዕለት ሰብአዊ ድጋፎች በተጨማሪ በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት የሰላም ሚኒስትሯ የዜጎችን ስነ ልቦና ለመጠበቅም የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)