በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ የፀጥታ አባላት እውቅና ተሰጠ

የፀጥታ አባላት

ነሐሴ 19/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ሀገርን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት በማክሸፍ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ለመታደግ የህይወት መስእዋትነት ለከፈሉ የፀጥታ ኃይሎች የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር እውቅና ሰጠ፡፡

በመርኃግብሩ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ ካሳሁን እምቢያለ ኢትዮጵያን ለመታደግ የህይወት መስእዋትነት የከፈሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች ታሪክ በክብር መዝገብ ላይ ስማቸውን ከትባ ታኖራቸዋለች ብለዋል፡፡

የአያት ቅድመ አያቶቻችንን የአደራ ሀገር ለማስቀጠል መስራት ይገባል ያሉት ከንቲባው የሀገርን መፍረስ እንዲሁም የዜጎችን መበተን ቋምጦ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን አሸባሪው የትሕነግ ቡድን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ እና የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖን ላበረከቱ የፀጥታ ኃይሎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል::

መተኪያ የሌላት ህይወታቸውን ሳይሳሱ ለሀገራቸው ከለላ ሆነው ያለፉ ጀግኖች ፈለግን በመከተል የሰላምን አማራጭ ረግጦ ዳግም ወደ ጦርነት የገባውን አሸባሪ ቡድን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ እንዲሰለፍ ጥሪ ቀርቧል::

ዜጎች አካባቢያቸውን በንቃት ከመጠበቅ እና ውስጣዊ ሰላም ከማስከበር ባለፈ ቁር ሳይል ሀሩር ሌት ሳይል ቀን ግንባር ለዘመተው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንዲያደርጉም ተጠይቋል::

የውስጥ አንድነትን በመናድ እኩይ ዓላማውን ከዳር ለማድረስ እየሰራ የሚገኘውን አሸባሪው የትሕነግ ቡድን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በሆነው ሕብረት በመታገዝ ትልሙን መቅበር ያሻል ነው የተባለው፡፡

ሔብሮን ዋልታው (ከደብረ ብርሃን)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW