በነሃሴ ወር የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ያለምንም ለውጥ ባለው ይቀጥላል ተባለ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የነሃሴ ወር የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ በሐምሌ ወር እየተሸጠበት ባለው ዋጋ ያለምንም ለውጥ እንደሚቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቀ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሐምሌ 23/2014 ዓ.ም እስከ ነሃሴ 30/2014 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚሆን የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ክለሳን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም ከሰኔ 29/2014 ዓ.ም ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራር በተመሳሳይ በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም እንደሚቀጥል ለዋልታ በላከው መግለጫ ገልጿል።

በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጪ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም እየተሸጠበት ባለው ዋጋ ያለምንም ለውጥ የሚቀጥል ሲሆን፤ ነገር ግን የአውሮፕላን ነዳጅን በሚመለከት በወቅታዊ የዓለም አቀፍ ዋጋ ተሰልቶ በመጣው አዲስ አበባ ላይ በሊትር 84 ብር ከ42 ሳ እንዲሸጥ የተወሰነ መሆኑን አስታውቋል።