በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃቶች በዘላቂነት ለመከላከል መንግሥት በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ተባለ

ሐምሌ 2/2014 (ዋልታ) የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኞች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በዘላቂነት ለመከላከል መንግሥት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ፡፡

በምዕራብ ወለጋ በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባው አስነዋሪ ጭፍጨፋ በንጹሃን ዜጎች ላይ መፈጸሙ ልብ ሰባሪ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጽንፈኞችና በሽብር ቡድኖች የሚፈጸሙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመግታትና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የችግሩን ምንጭ መረዳት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ዋነኛ የችግሩ ምንጭም አብሮነት እንዲሸረሸርና ኢትዮጵያ እንድትኮስስ ታስቦ ለዘመናት ሲሸረብ የቆየ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚንዱ ስራዎች ለዓመታት መሰራታቸውንና በምትካቸው ፅንፈኝነት ሲዘራ መቆየቱን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህም ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወንበት በመሆኑ ይህን በማደናቀፍ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትለማ ርብርብ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በቆሙባቸው ጊዜያት ሁሉ ፈተናዎቻቸውን በድል መወጣታቸውን አስታውሰው ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ማንበርከክ የሚቻለው የሕዝቦቿን አንድነት በመሸርሸር ነው የሚል አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሕዝብና መንግሥትን ለመነጠል ያለ እንቅልፍ እንደሚሰሩ ጠቁመው የመሪዎችን ንግግር ከአውድ ውጭ እየተረጎሙ ጭምር ችግር ለመፍጠር እንደሚሞክሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የፀጥታ መዋቅሩን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለመከፋፈልና ኢትዮጵያን ለማዳከም በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም የፀጥታ ኃይሉ ከኢትዮጵያዊነቱ ዝንፍ የማይል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን የጸጥታ አካል ለመገንባት ታስቦ የተተገበረው ሪፎርም ስኬታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል::

መንግሥት ለዴሞክራሲና ለሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያን ለማፅናት የተቋማት ግንባታ ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለሀገራዊ ድል በጋራ መቆም ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ተገንዝበው እጅ ለእጅ በመያያዝ የዳገቱን ጉዞ በስኬት እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW