በኖርዌይ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ1.3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ)- በኖርዌይ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብና የሲቪክ ማኅበራት አባላት ባካሄዱት የበይነ መረብ ውይይት በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የ1 ሚሊዮን 360 ሺህ ብር ድጋፍ አሰባሰቡ፡፡
በኖርዲክ ሀገራት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕከተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ባደረጉት ንግግር በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ተነሳሽነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ለሚያደርጉት ጥረት አመስግነዋል።
ኤምባሲው በቀጣይም ዳያስፖራውን በማስተባበር ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው “በአሸባሪው ህወሃትና ደጋፊዎቹ የውጭ ሃይሎች የተቃጣብንን ሃገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ ኢትዮጵያውያን በያሉበት በአንድነት ተነስተዋል” ብለዋል።
በሃገር ውስጥ ያሉ ዜጎች በተለይም ወጣቶች በከፍተኛ ቁጥር የክተት ጥሪውን በመቀበል ጦሩን በመቀላቀል ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ “ሌላው የህብረተሰብ ክፍልም ከፍተኛ ሃብት በማሰባሰብ ለመከላከያ ሃይላችን ደጀንነቱንና የሞራል ምንጭነቱን በማሳየት ላይ ይገኛል” ብለዋል።
በመላው ዓለም የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በያለበት በፐብሊክ ዲፕሎማሲና በሃብት ማሰባሰብ ተግባራት ላይ በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ በማሰባሰብ የታቀደውን አንድ ሚሊዮን ዶላርና ከዕቅድም በላይ የሆነ ሃብት ማሰባሰብ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይድሩስ ሀሰን በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልገው አብራርተዋል።
በኖርዌይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ችግሩን ለመቅረፍ የጀመሩት በጎ ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው የጠየቁት፡፡
በኖርዌይ በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተባበሪ ኮሚቴ አማካይነት በዕለቱ 272ሺህ የኖርዌጂያን ክሮነር ወይም 1 ሚሊዮን 360 ሺህ ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ አስተባባሪው ኮሚቴውና በኖርዌይ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት ለወደፊትም በተቻላቸው አቅም ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።