በኖርዌይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሙያተኞች ድርጅት ለዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ 91 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

በኖርዌይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሙያተኞች ድርጅት ለአምስት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ የሚውል 91 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ያደረገው “ኢትዮጵያን ኖርዌጃን ፕሮፌሽናል ኦርጋናይዜሽን” የተሰኘ ድርጅት ነው።

የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ ኖርዌይ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሸጋው አናጋው ድጋፉን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው የኖርዌይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ያዘጋጀውን ውድድር በማሸነፉ ያገኘውን ገንዘብ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኖርዌይ የተራድኦ ድርጅቱ በመላው ዓለም ለሚገኙ ታዳጊ አገራት የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን የኖርዌይ ገንዘብ (ክሮነር) የሚያሸልም ውድድር አውጥቶ እንደነበር ነው ያስታወሱት።

በውድድሩ ከተካፈሉት 199 አገራት መካከል ስልሳ የሚሆኑት ሽልማት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ኢትዮጵያን ወክሎ በወድድሩ የተካፈለው ‘በኖሮዌይ የኢትዮጵያ ሙያተኞች ድርጅት’ ከተሸላሚዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በውድድሩ 20 ሚሊየን ክሮነር ወይም 91 ሚሊየን ብር መሸለሙን ነው የገለጹት።

በሽልማቱ ያገኘውን ገንዘብ ለጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ደብረማርቆስና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የአቅም ግንባታ ስራ እንዲውል ድጋፍ ማድረጉንም ተባባሪ ፕሮፌሰር ሸጋው አንጋው የገለጹት። ድጋፉም በ6 ዓመት ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚሆን ነው የተናገሩት።

ልዩ ፍላጎት፣ሜዲካል ቴክኖሎጂ (ኢ ሄልዝ) እና ከኮምፒውተር ጋር የተገኛኙ የትምህርት ክፍሎች ደግሞ በድጋፉ ትኩረት የሚሰጥባቸው ዘርፎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪ ድርጅቱ 45 ለሚሆኑ የማስተርስ ተማሪዎች እና 15 የዶክትሬት ተማሪዎች በኖርዌይ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራ እንደሚያከናውም ተናግረዋል።

በኖርዌይ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና ምሁራን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ እንደሚደረግም ነው ያነሱት።

ድጋፉ በስራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስርዓተ ትምህርት ቀረፃን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም፣ ልማትና እድገት የሚያደርጉትን አወንታዊ አስተዋፆ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።