በአለታ ወንዶ የምርጫ ክልል ትላንት ተቋርጦ የነበረው የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ ቀጥሏል

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ የምርጫ ክልል ትላንት ተቋርጦ የነበረው የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ ከማለዳው 2፡30 ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡
ትላንት 8 :15 ጀምሮ ባጋጠመው የክልል ምክር ቤት ድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት የድምፅ መስጠት ሂደቱ ተቋርጦ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።
በአለታ ወንዶ ምርጫ ክልል ጨፌ ቀበሌ ቁጠባ ምርጫ ጣቢያ ለመራጭነት ተመዝግበው ከነበሩ 1ሺህ 11 ሰዎች መካከል 549 የሚሆኑት በትላንትናው እለት ድምፅ መስጠታቸውን የጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚ አቶ ተካልኝ መልከቶ ገልፀዋል።
ትላንት የተሠበሠበው የህዝብ ድምፅም ሁሉም አካላት በተሠበሠቡበት ተፈራርመው ታሽጎ ሲጠበቅ ማደሩንም አቶ ተካልኝን ጨምሮ የጣቢያው ታዛቢዎች እና አስፈፃሚዎች ተናግረዋል።
በዛሬው እለት 461 የሚሆኑት መራጮች ድምፃቸውን ለመስጠት ከማለዳው 1 ሰዓት ጀምሮ የተሰለፉ ሲሆን፣ ከ2:30 ጀምሮ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ተጀምሯል።
ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ትላንት መቋረጡ ምንም ችግር አልፈጠረብንም ዛሬም ድምፃችንን በመስጠት ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን መወጣት ችለናል ሲሉ ዋልታ ያነጋገራቸው ድምፅ ሠጪዎች ተናግረዋል።
(በድልአብ ለማ)