በአማራና በአፋር ክልሎች በህወሓት የሽብር ቡድን ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ500 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለፀ


ነሃሴ 20/2013 (ዋልታ) – በአማራና በአፋር ክልሎች በህወሓት የሽብር ቡድን ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ500 ሺህ በላይ መድረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ባለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የህወሓት የሽብር ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት ሳቢያ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ክልሉች ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ ቢሆንም በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰበት ህዝብ ቁጥር አንፃር የአጋር አካላት ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ወረራ የትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን አስቸጋሪ እንዳደረገው ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

የህወሓት የሽብር ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በቅርቡ ባደረሰው ጥቃት ሰዎችንና የቤት እንስሳትን ገሏል፤ ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟልም ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይም የተለያዩ ጥቃቶችን እያደረሰ በመሆኑ ስደተኞቹን በአማራ ክልል ለማስጠለል እየተሰራ መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል::