በአማራ ክልል በሕግ ማስከበር ሥራ የተያዙት ከ3500 በላይ የከዱ ሰራዊት ናቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 7/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በሕግ ማስከበር ሥራ የተያዙት መካከል ከ3500 በላይ የከዱ የሰራዊት አባላት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች በሰጡት ማብራሪያ ነው ይህንን የገለጹት፡፡

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና እየተስተዋለ ያለውን ሕገ ወጥነት ለማስተካከል የሕግ ማስከበር ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በሕግ ማስከበር ዘመቻው በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልል ሰፊ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

የሰላምና የውይይት አማራጮች ቀርቦላቸው ያልተፈቱ ችግሮች በክልል መንግሥታት በሚደረጉ የሕግ ማስከበር ኦፕሬሽኖች እየተፈቱ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል የፋኖን ስም በመጠቀም ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ቡድኖች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ አክቲቪስትና ጋዜጠኞች ሀገርን ለማፈራረስ ትክክል ያልሆነ ድርጊት ውስጥ እየገቡ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጋዜጠኝነት የከበረ ሙያ ቢሆንም የወሬ ፖለቲካ በመንዛት ችግር የሚፈጥሩ ጋዜጠኞችን እልባት እየሰጡ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጽንፈኝነትን የሚሰብክና ለጥፋት የሚቀሰቅስ ግለሰብ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው ጋዜጠኝነት የወንጀል መደበቂያ ሳይሆን የሀሳብ ምንጭ ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

የሕግ ማስከበር ኦፕሬሽኑ ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት በመሆኑ “አፈና” እየተባለ የሚወራው ከእውነት የራቀ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡