በአምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር የተመራ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድን ጂቡቲ ገባ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር የተመራ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑካን ቡድን ጂቡቲ ገብቷል።

የልዑካን ቡድኑ በጂቡቲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የአገሪቷ ግብርና ሚኒስትር አህመድ መሐመድ አዋሌህና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬና ሌሎች የኤምባሲው አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቡድኑ በጂቡቲ ቆይታው አፍሪካዊ ወንድማማችነትንና የጎረቤት ሀገር ወዳጅነትን የሚያጠናክሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራትን እንደሚያከናውን ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ከመላው አፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር በአረንጓዴ ዲፕሎማሲውም ለማስፋት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።

ዛሬ ጂቡቲ የገባው የወጣቶች የልዑካን ቡድን አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ማጠናከርን ያለመ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ያካሂዳል።

የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከጂቡቲ ተወካዮች ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱም ይጠበቃል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ከወጣቶች የተውጣጣ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑካን ለተመሳሳይ አላማ ደቡብ ሱዳን ጁባ መግባቱ ይታወቃል።

አረንጓዴ ዲፕሎማሲ አገራት በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ዘላቂ ልማት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የሚጠቀሙበት የዲፕሎማሲ እሳቤ ነው።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለጎረቤት አገራት ችግኝ በመስጠት ትብብሯን ለማጠናከር በመስራት ላይ ነች።