በአራት ወራት ከ123 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

ኅዳር 10/2014 (ዋልታ) በአራት ወራት ከ123 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስወቀ፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በአራት ወራት 133ቢሊየን 381ሚሊየን 680ሺሕ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነው 123ቢሊየን 962ሚሊየን 650ሺሕ ብር መሰብሰብ እንደተቻለና አፈጻጸሙም 92 ነጥብ 94 በመቶ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

እቅድ አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 ቢሊየን 334 ሚሊየን 850ሺሕ ብር ዕድገት ማሳየቱም ነው የተገለጸው፡፡ ይኸውም 15 ነጥብ 18 በመቶ ዕድገት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ገቢው የተሰበሰበውም ከሀገር ውስጥ ታክስ 80ቢሊየን 846ሚሊየን 400ሺሕ ብር እንዲሁም ከውጭ ንግድ ታክስና ቀረጥ 43ቢሊየን 116ሚሊየን 250ሺሕ ብር መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ገቢው በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ገቢን ለመሰብሰብ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተሰበሰበ በመሆኑ አፈፃፀሙ የተሻለ ሊባል የሚችል ነው ተብሏል፡፡

የተመዘገበው ስኬትም ግብር ከፋዮች ለአገራቸውና ለህዝባቸው በማሰብ በወቅቱና በትክክለኛው ጊዜ ግብራቸው አሳውቀው በመክፈላቸው እንዲሁም የሚኒስቴሩ እና የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮችና ሰራተኞችም ከምንጊዜውም በላይ የዕረፍት ጊዜአቸውን ጨምረው በቁርጠኝነት እና በትጋት መስራት በመቻላቸው የተገኘ ውጤት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡