በአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ስም የተሰየመው የአቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ

መስከረም 15/2014 (ዋልታ) አቢሲኒያ ባንክ በተባባሪ ፕሮፌሰር አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ስም 585ኛ ቅርንጫፉን ከፈተ።

የባንኩ ስያሜ ሀገራቸውን በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ከ60 ዓመታት በላይ ባገለገሉት እና ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረጉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰን ለመዘከር ያለመ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገር ባለውለታዎችን በማሰብ ረገድ ለሌሎችም መነቃቃትን ለመፍጠር ነው ተብሏል።

ባንኩ በአያት አዲስ መንደር ፊት ለፊት በሚገኝ ህንፃ ላይ የከፈተውን ቅርንጫፍም የባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ቤተሰቦች እንዲሁም የሙያ አጋሮቻቸው በተገኙበት ተመርቆ ሥራውን ጀምሯል።

ባንኩ በተለያዩ መስኮች ለሀገር በቆሙ ጀግኖች ስም ቅርንጫፎች እንዲሰየሙ በማድረግ ስማቸው እንዳይረሳና እንዲዘከር ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

የአቢሲነቢያ ባንክ የአንድ መቶ ሺሕ ብር ስጦታም ለቤተሰባቸው አበርክቷል።

ባንኩ ከ50 በላይ የሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የባለውለታዎች ሒሳብ በስራ ላይ ማዋሉም የሚታወስ ነው።

 

በትዕግስት ዘላለም