በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ገለጹ

ግንቦት 12/2013(ዋልታ) – የዞኑ ዓመታዊ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።ጉባኤው በአገራችን ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን በፀሎት ተጀምሯል።

በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ በሚያሰሩ አካላት ላይ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ በአገርቱ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ ያለውን ተግባር እንደሚደግፉ የሃይማኖት ተቋማት አባላት ገልፀዋል።

ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው ያሉት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላቱ ወጣቱ ትውልድ ለሰላም ዘብ መቆም አንደሚገባቸው አሳስበዋል።

6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ነፃ፣ፍትሐዊነና ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ምዕመናኑ በምርጫው ካርድ በመውሰድ የሚመራውን መንግስት በመምረጥ ዲሞክራሲያዊ መብቱን መጎናፀፍ እንዲችል ጥሪ ቀርቧል።

የሁሉም ቤተ-እምነት ተከታዮች በሰላም ዙሪያ በአስተምሮት፣በፀሎትና በተግሳጽ በማረም የሰላም እሴት ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ብጥብጥና ሁኬት የሚፀየፍ ዜጋ ለማፍራት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል። በመድረኩ በሰላም አብሮ-መኖር፣የህግ የበላይነት አስፈላጊነት እንዲሁም ስላማዊ ምርጫና የህብረተሰቡ ሚና በሚሉ ጉዳዮች ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካህዶበታል።

የሃይማኖት መቻቻልን መሠረት በማድረግ በአብያተ-ክርስቲያናት ውስጥ ችግሮች ስከሰቱ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የመፍታት እሴትን የማዳበሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በጉባኤው ተነስቷል። በቤተ-እምነቶች ዘንድ የዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን የኮቭድ-19  የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል አንፃር የሚታየው መዘናጋት ህብረተሰቡን ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም በጉባኤው ተመላክቷል።

የወላይታ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎኣ በጉባኤው ላይ እንዳሉት ሃይማኖት ተቋማት በሰሩት የሰላም እሴት ተግባር በዞኑ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም ጤናማ የፓለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር አስችሏል። በምርጫ ሽፋን አካባቢውንና አገርን በማፍረስ ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ በስውር ከውስጥና ውጭ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ሃይሎችን ለመከታተልና የሰላም አማራጭ ብቻ እንዲከታተሉ መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉ በጉባኤው ተጠቁሟል። የዞኑ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት በሰላም እሴት ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላስመዘገቡት የላቀ ውጤት ምስጋና አቅርበዋል።

6ኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሂደት ጤናማና ሰላማዊ እንዲሆን የሃይማኖት ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ርብርብ እንዲያደርጉ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገባው የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።