በአውደ ውጊያዎች ሠራዊቱን ላገለገሉ የህክምና ባለሙያዎችና ተቋማት እውቅና ተሰጠ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) የመከላከያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተለያየ አውደ-ውጊያዎች ላይ የተጎዱ የሠራዊት አባላትን ላገለገሉ የህክምና ባለሙያዎች እና ተቋማት እውቅና ሰጠ።
በመርኃግብሩ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ በጤና ዘርፉ ላይ የሚገኙ የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቢሾፍቱ ሆስፒታል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ተገኝ ለታ በወቅቱ እንደገለጹት በሙያቸው የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ እንዲሁም አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ እገዛዎችን ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው የአንድን ሀገር ኅልውና ለማስጠበቅ እና ሰራዊቱን ለማጠናከር የሕዝብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የጤና ተቋማትና ሙያተኞች የሕዝብ ደጀንነታቸውን በተግባር እንዳረጋገጡም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
እውቅና ከተሰጣቸው የህክምና ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር አንዷዓለም ደነቀ የህክምና ባለሙያዎች ሀገሪቱ ከእነሱ የምትፈልገውን ማንኛውንም ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።