በአይሲቲ ፓርክ በ130 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው “የሬድ ፎክስ” የመረጃ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ሳንዶካን ደበበ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በ130 ሚሊየን ዶላር የተገነባው “የሬድ ፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ” የመረጃ ማዕከልና ዋና መስሪያ ቤት በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

የአገልግሎት ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበን ጨምሮ የሬድፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አዳነ ካሳዬ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንቱን እውን ማድረጉ በዘርፉ በቂ እውቀት፣ ልምድ እና ፅናት ያለው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ትኩረት ከተሰጠባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቅሰው መሰል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና ለመደገፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ መቀጠሉን ማመላከታቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

“ሬድፎክስ” ዓላማው በተሟላ የመረጃ ማዕከል ግንባታ በዘርፉ የኢትዮጵያን አቅም ማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW