በአዲስ አበባ መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ኀዳር 12/2015 (ዋልታ) በመዲናዋ መሬትን አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ ውል የማቋረጥ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ አስተዳደር የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) በከተማ አስተዳደሩ ከመሬት ልማት ጋር በተያያዘ በሚታዩ ችግሮች ላይ እየተወሰዱ ስለሚገኙ እርምጃዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቢሮው ኃላፊው በዚህ ግዜ እንደተናገሩት፥ በአዲስ አበባ 90 ሄክታር መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሀብቶች ውል እንዲቋረጥ መደረጉን አንስተዋል።

ውል የተቋረጠባቸው መሬቶችን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ቀድሞ የተዘጋጁ መሬቶችን በማካተት በሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በግልጽ ጨረታ በማወዳደር ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

1 ሺህ 200 የሚሆኑ ግንባታቸው ጀምረው ያላጠናቀቁ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንዲያጠናቅቁ ከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ግንባታ ያልጀመሩ ግንባታ የመጀመሪያ ግዜያቸው ያላለፉ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ነው የገለፁት።

በመሬት ልማትና አስተዳደር ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን መለየቱንና ችግሩን በግዜያዊነት ብቻ ሳይሆን ከመሰረቱ ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን በዚሁ ግዜ ተናግረዋል።

በሰለሞን በየነ