በአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

ሚያዝያ 2/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተደራጀ መንገድ የመሬት ወረራ ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ግለሰቦቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 9 ቀጣና 3 ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጀርባ (አፓርታማ አካባቢ) በተደራጀ መንገድ በአካባቢ ጥበቃ ለአረንጓዴ ልማት በህጋዊ  ካርታ በተሰጠው ስፍራ በተለያየ ጊዜ በመግባትና ደን በመጨፍጨፍ በህገወጥ መንገድ መሬት ለመውረር ሲዘጋጁ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት 97 የሚደርሱ ግለሰቦች (20 ሴቶችና 77 ወንዶች) ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12፣ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 እና 6 የመጡ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በህገ ወጥ የመሬት ወረራው 150 የሚደርሱ ግለሰቦች እጃቸው ያለበት ሲሆን 10 ግለሰቦች በማለዳ በተካሄደው ኦፕሬሽን ማምለጣቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡