በአዳማ ከተማ ዜጎችን ከጎዳና ህይወት በዘላቂነት እንዲላቀቁ የሚያደርጉ 1 ሺህ ቤቶች ሊገነቡ ነው

ጫልቱ ሳኒ

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – በአዳማ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ጎዳናን መኖሪያ ያደረጉ ዜጎች ከጎዳና ህይወት በዘላቂነት እንዲላቀቁ የሚያደርጉ አንድ ሺህ ቤቶች ሊገነቡ ነው።

ለጎዳና ተዳዳሪዎች መኖሪያነት በሚገነቡት አንድ ሺህ ቤቶች የመሰረተ ድንጋይ ማኖሪያ መርኃግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የከተማ ክላስተር አስተባባሪ ጫልቱ ሳኒ በተለያዩ ዘርፎች መልካም ነገር ማድረግ የዜግነት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በአዳማ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ህይወት ለማላቀቅ የሚገነቡት አንድ ሺህ ቤቶች ከዜግነት ግዴታዎች መካከል የሚካተቱ መሆናቸው ጠቁመዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፣ ቤቶቹ በከተማዋ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎችን ከጎዳና ህይወት ከመታደጉ በተጨማሪ በከተማዋ በሚገኙ የፈረሱ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችንም ወደዚህ ስፍራ በማዘዋወር የተሻለ የመኖሪያ አካባቢ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

የሚገነቡ አንድ ሺህ ቤቶች በከተማዋ በሚገኙ መሀንዲሶች በጎ ፈቃድ ዲዛይናቸው የተሰራ ሲሆን፣ በዝቅተኛ የግንባታ ወጭ አንድ ቤት በ70 ሺህ ብር ይገነባል ተብሏል።

በቀጣይ ከሚገነቡት አንድ ሺህ ቤቶች መካከል በ4.5 ሚሊየን ብር የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ በበጎ ፈቃደኝነት ጥቂት ቤቶችን የሚሰራ ሲሆን፣ በግለሰቦችም ደረጃ በከተማዋ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ሰይድ አህመድ ኑር በአንድ ሚሊየን ብር 100 ቤቶችን ለመገንባት ቃል መግባታቸው ተገልጿል።

(በቁምነገር አህመድ)