በአፋር እና በአማራ ክልሎች የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን አጎራባች አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ውይይት ተካሄደ

 

በአፋር እና በአማራ ክልሎች የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን አጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሰላም የምክክር መድረክ በሰመራ ተካሄደ ፡፡

በሁለቱ ክልሎች የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን አጎራባች ዞን እና ወረዳዎች አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱም ህዝቦች የአመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ እና የሀይማኖት መሪዎች በተገኙበት የሰላም የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የሁለቱን ህዝቦች ሁለንተናዊ ቀረቤታ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እና ምክክር ተደርጓል፡፡

የአፋር ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ሁመድ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ትስስራቸው የጠነከረ አንድ ህዝቦች እና ቤተሰብም ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በአጎራባች አካባቢዎቻችን የተፈጠሩ ግጭቶችን በማስቆም ህዝቡን የሰላም እና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ብለዋል ፡፡

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን የከሚሴ ዞን አአስተዳደር አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው ግጭቶቹን ለመፍታት ትኩረት በመስጠት ህዝቡን የሚወክል አመራር ለመስጠት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የአመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ እና የሀይማኖት መሪዎች የችግሩ መነሻ ከሆኑት ውስጥ የአመራር ችግር፣ የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ንግድ እንዲሁም የእንስሳት ስርቆት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ፡፡

በሁለቱም በኩል ችግሩን የሚያባብሱት ጥገኛ አክቲቪስቶች፣ አንዳንድ አመራሮች እና የጸረ ሰላም አስፈጻሚ ጥቅመኛ ግለሰቦች በተለይ ከጁንታው ጋር ትስስር ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ የመፍትሄ ሀሳብም አቅርበዋል ፡፡

በቀጣይ ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ችግሩን ከአመራር አካላት ጋር በጋራ ለመፍታት ቃል መገባቱን ከአፋር ብዙሀን መገናኛ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል