በአፋር ከ40 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸው ተነገረ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል ከ40 ሺሕ በላይ ተማሪዎች እስካሁን ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ደረሳ መሀመድ እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት ከተፈናቀሉ ተማሪዎች መካከል ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው።

ከጦርነቱ በፊት ከ90 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደነበሩ የጠቀሱት ኃላፊው ከ40 ሺሕ በላይ የሚሆኑት እስካሁን እንዳልተመለሱ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱት ትምህርት ቤቶቻቸው በመፍረሳቸው፣ የውሃ፣ የመመገቢያ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶቻቸው በመውደማቸው ነው ተብሏል።

በጦርነቱ በነበረው ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድምጽና በትምህርት ቤቶቹ ያዩዋቸው ነገሮች የፈጠሩባቸው ሥነልቦናዊና ችግሮች የመማር ፍላጎት እንዲያጡና ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ እንዳደረጋቸው ተነግሯል።

ቢሮው ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችና ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

የትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ሥነልቦናዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለማቃለል በጦርነት ቀጣና ውስጥ ለነበሩ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡