በአፋር ክልል ሶስት ቀበሌዎች የጎርፍ አደጋ ተከሰተ

ነሐሴ 3/2013(ዋልታ) – በአፋር ክልል አዉሲ-ረሱዞን አይሳኢታ ወረዳ በአዋሽ ወንዝ ሙላት በሦስት ቀበሌዎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሀፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የቅድመ-ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ለኢዜአ እንደተናገሩት ከሃምሌ 28/2013 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳዉ ሦስት ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ሰብሮ በመውጣት ጎርፍ አስከትሏል።

“አደጋው ቀድሞ በተከናወኑ የቅድመ-ጥንቃቄ ስራዎች ህብረተሰቡ ከአካባቢዉ እንዲወጣ በመደረጉ የተፈናቀሉ ሰዎች ከመቶ አባዋራዎች የማይበልጡ ሲሆን በተጨማሪም ጎርፉ 50 ሄክታር መሬት በሚሆን የእርሻ መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል” ብለዋል።

ጎርፍ የተከሰተባቸዉ ቀበሌዎች የከርቡዳ፣ ኮሎዱራና ሂነሌ ቀበሌዎች ሲሆኑ ጎርፉ የሰበረበትን አካባቢ ለመዝጋት ከሚመለከተዉ የተፋሰስ ባለሰልጣን ጋር በመሆን ርብርብ እየተደረገ ነዉ” ብለዋል።

በክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ እየተመዘገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክልሉ የአዋሽ ወንዝን ተከትለዉ በሚገኙ 10 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ እንደሚከሰት ይጠበቃል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ቀደም ሲል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በተለይም በነዚህ ወረዳዎች ስር የሚገኙ 40 ቀበሌዎችን ጨምሮ ከአጎራባች ከፍተኛ ቦታዎች በሚነሱ ተፋሰሶች ምክንያት በነዚህ አካባቢዎች ከ90ሺ ሰዎች በላይ የጎርፍ ተጠቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።