በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገለጸ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ጤና ቢሮ እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺሕ በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ገልጿል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ሕጻናት ክትባት ዳይሬክተር አወል ጉደሌ አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች መሰባሰባቸውንና የሕጻናት ክትባት ሥራው በመስተጓጎሉ ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በሽታውን ቀድሞ መከላከልን ታሳቢ በማድረግ ከግንቦት 10 እስከ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺሕ በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ክትባቱ በጤና ተቋማትና በተመረጡ ቦታዎች እንደሚሰጥና የክልሉ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎች ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኩፍኝ ሚዝል በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ሲሆን በሽታው በወቅቱ ካልታከመ የዓይን ብርሃን ማጣት፣ ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል እብጠትና ተያያዥ ኢንፌክሽን ያጋልጣል።

በሽታው በየትኛውም እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም በተለይም ሕጻናት በተለየ ሁኔታ እንደሚያጠቃ ይነገራል።